Merid Negussie (Major General) : 1934-1989
  • Home
    • መርዕድ ንጉሤ | Merid Negussie (Bio Amharic)
    • Biography(English)
  • Events
  • Excerpts from the book
  • General Merid's Notes
  • Book Reviews and Comments
  • Contact us
Picture

መርዕድ ንጉሤ (ሜጀር ጄኔራል) ፤ 1926-1981

 ሜጀር ጄኔራል መርዕድ ንጉሤ ጥር 13 1926 ዓ.ም. በዘመኑ በነበረው የአስተዳደር መዋቅር በሸዋ ጠቅላይ ግዛት በሱሉልታ ወረዳ በሙሎ ምክትል ወረዳ ድሬ ለኩ በመባል በምትታወቀዋ መንደር ተወለዱ። ያችን የተወለዱባትን የገጠር መንደር ለቀው ዘመናዊ ትምህርት ለመማር እስከሄዱ ድረስ የወላጆቻቸውን ከብቶች በመጠበቅ፣ ፈረሶችን በመግራትና አንዳንድ የግብርና ሥራዎችን በመሥራት ያደጉበትን መልካምና ደግ ቤተሰብ ይረዱ ነበር።

 ጄኔራል መርዕድ በመጀመሪያ ወሊሶ ከዚያም አዲስ አበባ በበየነ መርዕድና በኮከበ ጽባሕ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች ትምህርታቸውን ተከታትለዋል። በክብር ዘበኛ አካዳሚ ለሦስት ዓመታት በእጩ መኮንንነት ከሠለጠኑ በኋላ በ1946 ዓ.ም. በምክትል መቶ አለቅነት ማዕረግ ተመርቀው ሲወጡ ለረጅም ዓመታት አብረዋቸው ከኖሩት ከባለቤታቸው ከወይዘሮ አሰለፈች ኃይለማርያም ጋር ትዳር መሥርተዋል። በ1944 ዓ.ም. የክብር ዘበኛ ሠራዊትን የተቀላቀሉት ሜጄር ጄኔራል መርዕድ ንጉሤ ለ37 ዓመታት በሲቪልና በወታደራዊ ኃላፊነቶች አገራቸውን አገልግለዋል።

 በውትድርና ሕይወታቸው መጀመሪያ በክበር ዘበኛ ሠራዊት ውስጥ የመቶ መሪ ከዚያም ኮንጎ በተባበሩት መንግሥታት ጸጥታ አስከባሪ ጦር ረዳት የዘመቻ መኮንን በመሆን ሠርተዋል። ኮንጎ በነበሩበት ጊዜ በጄኔራል መንግሥቱና በወንድማቸው በገርማሜ ነዋይ ንጉሠ ነገሥቱን ከሥልጣን ለማውረድ የተደረገው የመፈቅለ መንግሥት ሙከራ ሳይሳካ ይቀራል። ከመፈንቅለ መንግሥቱ መክሸፍ በኋላ የክብር ዘበኛ ጦር አባላት በእሥራትና በግዞት እንዲቀጡ ሲበየን የተለየ አቋምና አስተዳደር የነበረው የክብር ዘበኛም እንደ ሌሎቹ ክፍለ ጦሮች በምድር ጦር ሥር እንዲሆን ተወሰነ። አዲስ አበባ ስላልነበሩ ከእሥርና ከግዞት የተረፉት የክብር ዘበኛ ሠራዊት አባሎችም ከልዩ ክትትልና እንግልት ሊያመልጡ አልቻሉም። የዚያን ጊዜው መቶ አለቃ መርዕድም ከኮንጎ እንደተመለሱ በቅጣት ወደ ኤርትራ ተላኩ።

በወታደራዊ አገልግሎት ዘመናቸው ከኤርትራ መልስ ደብረዘይት የአየር ወለድና የኮማንዶ ትምህርት ኮርስ ከተከታተሉ በኋላ በፍቼ የማሠልጠኛ ጣቢያ በአዛዥነት ከዚያም ሆለታ በሚገኘው የአዛዥነትና መምሪያ መኮንንነት ኮሌጅ ውስጥ በተማሪነት፣ በአስተማሪነትና በአስተዳዳሪነት ሠርተዋል። ቀጥሎም በአዲስ አበባ የአራተኛ ክፍለ ጦር የትምህርት መኮንን፣ በባሌ የክፍለ ጦሩ ቀዳሚ መምሪያ የዘመቻ መኮንን ከዚያም ነገሌ ቦረና የሚገኘው የ28ኛ ሻለቃ አዛዥ በመሆን አገልግለዋል።

በ1966 የነገሌው ጦር ሲያምፅ ጦሩን ከጀርባ ሆነው በመቀስቀስና በመምራት ከፍተኛ አስተዋፆ አድርገዋል። በዚሁ ዓመት አጋማሽ ወደ አዲስ አበባ በመዛወር የ1966 ዓ.ም. ሕዝባዊ ዐመፅ እየተስፋፋ በሄደበት ወቅት የ4ኛ ክፍለ ጦር የዘመቻ መኮንን ሆነው ሠርተዋል። የ4ኛ ክፍለ ጦር የዘመቻ መኮንን እያሉ ጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር በመባል የሚታወቀው የተለያዩ የጦር ክፍሎች ተወካዮች የሚገኙበት “ደርግ” ተቋቋመ። ደርግ ሲቋቋም ጄኔራል መርዕድ (ያን ጊዜ ሌ/ኮሎኔል) ከ1966 እስከ 1969 ዓ.ም. የደርጉ ሥራ አስፈጻሚ ሹም በመሆን አገልግለዋል።

አገራችን በሶማሊያ ወረራና በሻዕቢያና ጀብሃ የመንገጠል እንቅስቃሴ በተወጠረችበት ወቅት የያኔው ኮሎኔል መርዕድ 7ኛ ክፍለ ጦር የሚል ስያሜ ያገኘውን ጦር በአጭር ጊዜ ውስጥ አሠልጥነው፣ ለውጊያ አዘጋጅተው የዚሁ ክፍለ ጦር አዛዥ በመሆን ኤርትራ ዘምተዋል። ይህንን ክፍለ ጦር እየመሩ በተደረገ ውጊያ የመቁሰል አደጋ ደርሶባቸዋል። ከሕክምና መልስም የሰሜን እዝ ዋና አዛዥ በመሆን ጦሩን መርተዋል። የሰሜን እዝ አዛዥ በነበሩበት ወቅት በምጽዋና በሌሎች የጦር ሜዳዎች ላይ ባሳዩት ጀግንነትና የአመራር ብቃት በደርግ ዘመን የመጀመሪያው ብርጋዴር ጄኔራል ሆነው ለመሾምና የአንደኛ ደረጃ የጀብዱ ሜዳልያ ተሸላሚ ለመሆን በቅተዋል።

ከሰሜን እዝ አዛዥነታቸው በመቀጠል የኢትዮጵያ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም በመሆን አገልግለዋል። በዚህ የሥራ ኃላፊነታቸው ላይ የሶማሊያን ጦር ርዝራዥ ከኢትዮጵያ ምድር ጠራርጎ ያወጣውን የ“ላሽ” ዘመቻን በተሳካ ሁኔታ መርተዋል።እንዲሁም ለኢትዮጵያ ጦር ኃይሎች ከፍተኛ ጠቀሜታ ያላቸው መመሪያዎችን አዘጋጅተዋል።
ጄኔራል መርዕድ የኢትዮጵያ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ሆነው በመሥራት ላይ እያሉ በተፈጠረ ውዝግብ ለተወሰነ ጊዜ በጡረታ እንዲገለሉ ከተደረገ በኋላ በሲቪልነት የሐረርጌ ከዚያም የኤርትራ ክፍለ አገር ዋና አስተዳዳሪ ሆነው በተከታታይ አገልግለዋል።

የኤርትራ ክፍለ አገር አስተዳዳሪ ሆነው እየሠሩ ሳለ በተጨማሪ በሜጀር ጄኔራልነት ማዕረግ በሰሜን ኢትዮጵያ የሰፈረው የሁለተኛው አብዮታዊ ሠራዊት ዋና አዛዥ ሆነው ለአራት ዓመታት ሠርተዋል። በዚህ ጥንድ ኃላፊነታቸውም ወቅት በኤርትራ ክፍለ አገር ሰላም እንዲሰፍንና የሕዝቡ ኑሮ እንዲሻሻል የሚመለከታቸውን አካላትና ያገር ሽማግሌዎችን በማነጋገር ጉዳዩን በሰላም ለመፍታት ያደረጉት ጥረት በደርግ ውስጥ በነበሩ ከፍተኛ ሹማምንት ተቃዋሚነት ተጨናግፏል።

ከኤርትራ በኋላ ለሁለተኛ ጊዜ የኢትዮጵያ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም በመሆን ወደ አዲስ አበባ ተመለሱ። የጦር ኃይሎች ኤታማዦር ሹም ሆነው በማገልገል ላይ እያሉ የአገሪቱን ውድቀትና በመንግሥት በኩል ያሉ ስሕተቶችን የሚጠቁም የትክክለኛውን ጎዳና መፍትሔ ሐሳቦችን በተለያዩ ስብሰባዎችና ሪፖርቶችን ቢያቀርቡም ሰሚ ማግኘት አልቻሉም። በዚህም ምክንያት በአገሪቱ አስተዳደርና በጦር ኃይሎች አመራር ላይ ከኮሎኔል መንግሥቱ ጋር ያላቸው ቅራኔ እየተባባሰ መጣ።

ጄኔራል መርዕድ ንጉሤ የኮሎኔል መንግሥቱን የደርግ መንግሥት ለመጣልና በአገሪቱ ሰላም እንዲሰፍን ለማድረግ የታቀደውን የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ በግንባር ቀደምትነት መርተዋል። የመፈንቅለ መንግሥቱ ሙከራ ሲከሽፍ እጄን አልሰጥም ብለው እጅግ በሚወዷት አገራቸው ሰንደቅ ዓላማ ተሸፍነው ግንቦት 8 ቀን 1981 ዓ.ም. ራሳቸውን ሠውተዋል።

​ጄኔራል መርዕድ ንጉሴ ትሑት፣ ሰው ወዳድና አክባሪ፣ ፍቅር ሰጥተው የማይጠግቡ ደግ አባት ነበሩ። ያን ፍቅር በክብር ተቀብለው ያባታቸውን ፈር ለመከተል የሚጥሩ አምስት ሴት፣ አራት ወንድ ልጆች እንዲሁም አስራ ሰባት የልጅ ልጆችን አፍርተዋል።


Picture
                                   እባክዎን አስተያየቶንና ጥያቄዎን በኢሜል ይላኩልን  info@meridnegussie.com
እኛን ለማግኘት በማንኛውም ጊዜ ይጻፉልን ፣ በደስታ እንመልስልዎታለን ​።
Proudly powered by Weebly
  • Home
    • መርዕድ ንጉሤ | Merid Negussie (Bio Amharic)
    • Biography(English)
  • Events
  • Excerpts from the book
  • General Merid's Notes
  • Book Reviews and Comments
  • Contact us