Merid Negussie (Major General) : 1934-1989
  • Home
    • መርዕድ ንጉሤ | Merid Negussie (Bio Amharic)
    • Biography(English)
  • Events
  • Excerpts from the book
  • General Merid's Notes
  • Book Reviews and Comments
  • Contact us
Picture

ከመጽሐፉ የተወሰደ    

​ 
                                                                                        እማማ ሃደ ኩሊ
    አባታችን እንኳን ስለልጅነቱ ቀርቶ ሕይወቱን ሙሉ ስላጋጠመውና ስላሳለፈው ሲያወራን ሃደ ኩሊን ሳያነሣ ማለፍ አይችልም ነበር። የአባታችን ሞግዚት ሃደ ኩሊ ሙሉ ስሟ ዋሪቴ ደበሉ ነው። አገር ምድሩ የሚጠራት ሃደ ኩሊ (በኦሮምኛ “የኩሊ እናት”) እያለ ነበር፤ አባታችን ደግሞ “እማማ” እያለ ያሳ ምራታል።
ሃደ ኩሊ ከአባታችን ሌላ ሁለት ወንድሞቹን (ጉግሣንና ግርማን) አሳድጋለች። አባታችን ባይቀበለውም ከሌሎቹ ሁሉ ለእርሱ እንደምታዳላ በግልጽ ይታወቅ ነበር። ሃደ ኩሊ በኃላፊነት የተሰጧትን ልጆች ከመንከባከብ በላይ ሥርዓትን በማስተማር ትታወቅ ነበር። አቶ ንጉሤና ወ/ሮ ፈለቀች በራሳቸው ልጆች ጉዳይ ጣልቃ ገብተው አንዳች አስተያየት እንዲሰጡ ወይንም ውሳኔ እንዲወስኑ አትፈቅድም ነበር። እንግዳ እንኳን መጥቶ ልጆቹ ቀርበው እጅ ይንሱ ሲባል የእሷ ፈቃድ መጨመር ነበረበት። አጎታችን ጋሽ ጉግሣ “እቤታችን እንግዳ ሲመጣ እንኳን እጅ ለመንሳት እሷ ፈቅዳ ነው የምንሄደው። ‘ሂዱና እንግዳ የተባለውን ሰው ሳሙና ቶሎ ተመለሱ’ ትለናለች። ወላጆቻችንም ያከብሯታል” በማለት አጫውቶናል። አባታችን ስለእሷ ተናግሮ አይጠግብም። ስለ ሃደ ኩሊ እንደሚያወራ እያወቅንም በማሾፍ መልክ “ማንን ማለትህ ነው? ስለማን ነው?” ብለን እንጠይቀዋለን። ስሟን ደጋግሞ በመጥራቱ ተመልሳ ትመጣለት ይመስል “ሌላ ማን ይሆናል…እማማ ናታ!” ሲል ድምጹ ላይ ያለው ቀለም ከልብ ይወዳት እንደነበረ በግልጽ ያስታውቃል።
ሃደ ኩሊን እሱ ብቻውን አውቋት፣ እሱ ብቻውን ወዷት፣ እሱ ብቻውን አድንቋት እንድትቀር አልፈለገም። በእሱ ማንነት ውስጥ ያላት ቦታ እንዲታወቅላት ስለፈለገ በራሱ የእጅ ጽሑፍ ለእሷ ያለውን ፍቅርና አክብሮት ሲገልጽ…
ሞግዚቴ (እማማ ሃደ ኩሊ) እኔና ወንድሞቼን አሳድጋናለች። እማማ ከኦሮምኛ ቋንቋ ሌላ የማትናገር፣ ገጠር ተፈጥራ ገጠር ያደገች፣ እስከመጨረሻውም የኖረች ሲሆን የግንዛቤዋ ሁኔታ ከፍተኛ ነው። በሕፃንነቴና በወጣትነት ዕድሜዬ ስትነግረኝ የነበረው እስከ ዛሬ በሕሊናዬ ውስጥ ቦታ አለው። ጥቂቶቹን ብጠቅስ ከቤት ስወጣ ሁልጊዜ ዱላ እንድይዝ ታስገድደኝ ነበር። “ባዶ እጅ ያስጠቃል፣ ስትመታም ብልት አይተህ ነው። ከብልቶች አንዱ ቁርጭምጭሚት ነው፤ ቁርጭምጭሚቱን ደኅና አድርገህ ካበሰልክ ሊከተልህ አይችልም፤ እኔ ዘንድ ከደረስክ እኔ አለሁልህ” ትለኛለች።
“ከልጆች ስትጣላ እንዳትቀደም፤ ድንገት ቢቀድሙህና ቢያምህም ጨክን እንጂ አታልቅስ፤ ካለቀስክ ይደፍሩሃል” ትለኛለች። ውጪ ቆይቼ ስመጣ “ሰዎች ምን አወሩ?” ትለኛለች። ገና መናገር ስጀምርና የተናገሩትን ሰዎች ስጠራ የማይረቡ ሰዎች መስለው ከታዩዋት “እነሱን ተዋቸው ቦተሊከኛ (ወሬኞች) ናቸው” ትለኛለች። ደኅና ሰዎች ከመሰሏት እስከመጨረሻው ካዳመጠችኝ በኋላ “ሌላም ቀን አዳምጣቸው” ትለኛለች። ከዚህ ሌላ ማታ ማታ እሳት እየሞቅን ስለአካባቢያችን ብዙ ነገር ትነግረኛለች። ሁሉን ነገር ካለች በኋላ “ትሸነፉና ልብ አድርጉ፣ መሸነፍ ነውር ነው። እናንተ ወተት እየጠጣችሁ ጎመን የሚበሉ ልጆች ካሸነፏችሁ ዋጋችሁን ነው የምሰጣችሁ” ትለናለች። እውነትም አልቅሰን ከገባን መግቢያ የለንም። በጉሜዋ6 ትከሰክሰናለች።
…እማማ እኮ ብዙ ነገር አስተምራኛለች። “ራስን ከመቻል የበለጠ ነገር የለምና ታግለህ ራስህን ቻል። የመጣው ይመጣል እንጂ ልጄን ማንም አይነካውም። እሺ እቴ ብርድ ከማንቀጥቀጥ ሌላ ምን ያመጣል? ከውርደት የበለጠ ምን ሞት አለ? ቁምነገር የማይሠራ ሰው ያለመፈጠሩ ይሻላል። ውሸታቸውን ነው እንጂ በርኖስ ለባሾችም ይበርዳቸዋል። በሰፈሩት ቁና መሰፈር አይቀርም። ለሁሉም ጊዜው አለው” በሚሉ ምሳሌዎች እየተነሣች አንዴ በማባበል አንዴም በማጋጨት ታስረዳኝና ታስተምረኝ የነበረው ሁሉ ትዝ ይለኛል። አብዛኛውንም ማመዛዘንና መገንዘብ የቻልኩት በኋላ ነው።

Picture
                              የሦስተኛው ኮርስ ዕጩ መኮንኖች ሥልጠና

ወጣቱ መርዕድና ታላቅ ወንድሙ ተፈራ ንጉሤ ለውትድርና ምልመላ የወጣውን ማስታወቂያ በማየት ከተመዘገቡ በኋላ የተሰጠውን ፈተና አለፉ። የጤና ምርመራ ተደርጎላቸው ለወታደራዊ ሥልጠናና ግዴታ ብቁ መሆናቸውም ተረጋገጠ። የጦር ትምህርት ቤቱ የሚከፈተው በሚቀጥለው ዓመት መስከረም 20 ቀን 1944 ዓ.ም. ስለነበር ወንድማማቾቹ የክረምቱን ጊዜ ከወላጆቻቸውና ከቤተዘመድ ጋር ለማሳለፍ ወደ ሙሎ ሄደው እዚያው ሲዝናኑ ከረሙ። አንዳንድ የቤተሰብ አባላት መርዕድና ተፈራ ወታደሮች ከሆኑ ጦር ሜዳ ተልከው ይሞቱብናል ብለው በመሥጋት ውትድርናቸውን ባይወዱትም አብዛኛው ቤተዘመድና ወላጆቻቸው ልጆቻቸውበሚመኙትና በሚጓጉለት የውትድርና የሙያ መስክ ውስጥ በመግባታቸው ተደሰቱ።

በዚህ ዓይነት ክረምቱን ያሳለፉት ወንድማማቾቹ በቀጣዩ ዓመት መጀመሪያ ወር የዋለውንም የመስቀልን በዓል ያከበሩት እዚያው ሙሎ ነበር። አያታችን አካከዩ ጥርኝና ዳማ የሚባሉ ምርጥ ምርጥ ፈረሶች ስለነበሯቸው አባታችንና ጋሽ ተፈራ ከዘመዶቻቸውና ከአብሮ አደግ ጓደኞቻቸው ጋር በበዓሉ ላይ የፈረስ ጉግሥ ሲጫወቱና ሲዝናኑ ዋሉ። ከዚህ የመንፈስ ዕረፍት በኋላ ነበር አዲስ አበባ በመምጣት ወደ ጦር ትምህርት ቤቱ ማሠልጠኛ ተቋም የገቡትና የቀደምት አባቶቻቸውን ዓርማ አንግበው አገርና ወገንን የማገልገል ተልዕኮን “ሀ” በማለት የጀመሩት። አባታችን የዚያን ዝነኛ የጦር ትምህርት ቤት ቆይታውን ትዝታ በማስታወሻው ላይ እንዲህ ሲል ይገልጸዋል።

በዕጩ መኮንንነት የቆየሁት 2 ዓመት ከ8 ወር ሲሆን የትምህርት ቤቱ ዋና አስተማሪዎች ስዊድኖች ሲሆኑ ረዳቶቹ ኢትዮጵያውያን መኮንኖች ናቸው። ትምህርቱ ይሰጥ የነበረው በእንግሊዝኛ ቋንቋ ሲሆን የቋንቋ ችግር ነበረብን። የማይታበልና ጠቃሚ ሆኖ የተገኘውም የሚሰጡት ትምህርቶች እጅግ ዝርዝርከመሆናቸውም ሌላ ዕጩ መኮንኑ ፍጹም እስኪገባው ድረስ በቲዎሪና በድርጊት ስለሚማር አንዳችም ነገር አያመልጠውም። በትምህርቱ አሰጣጥና ጥንቃቄ የተነሣ ደንቆሮና እውርም ሊረዳ ይችላል ለማለት ያስደፍራል። ትምህርት ቤቱ ለመግባት የሚፈቀደው ከ18 ዓመት ዕድሜ ጀምሮ ቢሆንም የኔ ዕድሜ ያኔ 17 ነበር፤ ፎርሙ ላይ የሞላሁት ግን 18 ብዬ ነው። ትምህርቱን የምከታተለው ፈተና ላለመውደቅ እንጂ ይጠብቀኝ ከነበረው ኃላፊነት ጋር አገናዝቤ አይደለም። ፈተና የማለፉን አስፈላጊነት እንጂ ቀደምት (ሲኔሪይቲ) የሚባለውን አላውቅም፤ በመሆኑም አላስብበትም ነበር። በመሆኑም ጎበዝ ከሚባሉት ዕጩ መኮንኖች መካከል አልነበርኩም። በጊዜው የነበርነው ዕጩ መኮንኖች ከፍተኛ የሆነ ወታደራዊ መንፈስ ነበረን። ለዚህ ዋና ምክንያት የሆነው በ1943 ዓ.ም. ከክብር ዘበኛ ሠራዊት አንዳንድ ሻለቃ ወደ ደቡብ ኮሪያ ይዘምት ስለነበርና የዚያ ሠራዊት ዝና እጅግ የገነነና ተወዳጅ በመሆኑ ነው። ከዚህም ሌላ በዚያ ጦርነት ላይ የነበሩት መኮንኖች ከጦር ሜዳው የቀሰሙትን ልምድና ጦርነቱን በአሸናፊነት ለመወጣት በጦር ሜዳ አካባቢ የሚሰጣቸውን ልምዶች ለእኛ ለዕጩ መኮንኖች ገለጻ ያደርጉ ስለነበር ነው።

አባታችን ቀደም ሲል ያነሣውን የእንግሊዝኛ ቋንቋ ጉዳይ በተመለከተ፦
​
…በየሳምንቱ ሰኞ ሰኞ ማንኛውም ዕጩ መኮንን በአማርኛ ቋንቋ እንዲናገር አይፈቀድለትም። ቁጥጥሩም እንደሚከተለው ይፈጸማል። ሦስት ካርዶች ለሦስት የሳምንት ኃላፊ ዕጩ መኮንኖች ይሰጣሉ። በእነዚህ ካርዶች ላይ “I hate to be on guilty’s neck” ተብሎ ተጽፎባቸው ማንጠልጠያ ሲባጎም ተሠርቶላቸዋል። ካርዱን የያዘው ዕጩ መኮንን በአማርኛ መናገር ይፈቀድለታል። ካርዱን ከራሱ ለማሳለፍ በድንገት አንዱን ዕጩ መኮንን በአማርኛ ያናግራል። ሌላው ዕጩ መኮንን ረስቶ በአማርኛ ከመለሰ ካርዱ ወደ እርሱ ተላልፎ አንገቱ ላይ እንዲንጠለጠል ይደረጋል። ከዚያም እርሱም በተራው ሌላ ዕጩ መኮንን በአማርኛ እስኪመልስለት አንጠልጥሎ ይዞራል። ይህ እንቅስቃሴ እስከ ምሽቱ 3 ሰዓት ይቀጥላል። እስከ ምሽቱ 3 ሰዓት ማስተላለፍ ያልቻለው ዕጩ መኮንን በቀጣዩ ቅዳሜና እሑድ ከግቢ መውጣት አይፈቀድለትም። ከግቢ መውጣት መከልከል እንደትልቅ ቅጣት ይታያል። ይሄ ዘዴ ዕጩ መኮንኖቹ የእንግሊዝኛ እውቀታቸውን እንዲያሳድጉ ተብሎ የታቀደ ነበር። 

በማለት አጎታችን ጋሽ ተፈራ አጫውቶናል። ዕጩ መኮንን መርዕድ በዚያ የጦር ትምህርት ቤት የሚሰጠውን የወታደራዊ ሳይንስ፣ መደበኛ የአካዳሚክ ትምህርት፣ የአስተዳደርና የአመራር ጥበብ፣ የአካላዊ ብቃት፣ የሥነ-ሥርዓት አጠባበቅና የመሳሰሉትን እውቀቶች እየተከታተለ እያለ ከኮሪያ ዘማቾች ጋር የሚያገናኘው ሌላ ጉዳይ አጋጠመው። ይህንን አጋጣሚ “በ1945 ዓ.ም. ወደ ኮሪያ እንዲሄድ ለተመረጠው ጦር በኮርስ ላይ የነበርነው ዕጩ መኮንኖች በረዳት አሠልጣኝነት ለሦስት ወር እንድንሠራ በመደረጉ ኃላፊነትና ዝግጅት መምራትና ማዘዝን ይበልጥ እንድማር አድርጎኛል”
​ ሲል ያስታውሰዋል።

​

                                    እባክዎን አስተያየቶንና ጥያቄዎን በኢሜል ይላኩልን  info@meridnegussie.com
Proudly powered by Weebly
  • Home
    • መርዕድ ንጉሤ | Merid Negussie (Bio Amharic)
    • Biography(English)
  • Events
  • Excerpts from the book
  • General Merid's Notes
  • Book Reviews and Comments
  • Contact us